የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

Published by Biniam Zewdie on

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባንኩ ያደረገውን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ልማቶች የፋይናንስ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር በየጊዜው ለሚቀርቡ የልማት ፕሮጀክት ጥሪዎች ፈጣንና ከፍተኛ መጠን ያለውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቅ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ባንኩ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ማኔጅመንቱና መላው ሰራተኛ ላደረገው የገንዘብ ድጋፍም ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እንዳሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ላቀረቡት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የልማት ጥሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚውን ድርሻ ወስዶ ምላሽ መስጠቱ የሚያስመሰግንና ከአንድ ትልቅ የፋይናንስ ተቋም የሚጠበቅ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው “ለቀረበው የልማት ተሳትፎ ጥሪ ወቅታዊና ባንኩን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት በመቻላችን ኩራት ይሰማናል። ይህ ሁሉ ሊሳካ የቻለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በቦርዱ፣ በማኔጅመንቱና በሰራተኛው ያላሰለሰ ተሳትፎ ነውና ምስጋና ይገባቸዋል” ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በግንባታ ሂደት ላይም ሆነ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ለበርካቶች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ የሀገርን ገፅታ የሚቀይሩና የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ማሳያ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ነው አቶ አቤ የገለፁት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች መሰረታዊ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኦላኒ ሳቀታ እንዳሉት ደግሞ ሰራተኛው ለሀገራዊ የልማት ጥሪዎች የሚያደርገው ተሳትፎ የላቀ መሆኑን አስታውሰው በገበታ ለሀገር ጥሪ ላይም የራሱን አሻራ ለማኖር የሚያስችለውን ምላሽ በዚህ መልኩ ማድረጉ ደስታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም ሸገርን ለማስዋብ ፕሮጀክት የ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያደረገው የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ የጎርጎራ፣ የወንጪ እና የኮይሻን ፕሮጀክቶች በማልማት ቱሪዝምን ለማስፋፋት ለተነደፈ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የሚውል ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የጤና፣ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ለአገራችን ልማትና ብልጽግና የቆመ መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ አገራዊ ባንክ ነው።

በተለይ ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ሲሰራ ቆይቷል። በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በቢሾፍቱ፣ በእንጦጦ፣ ገፈርሳና ሰበታ አካባቢዎች በየዓመቱ በርካታ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ለወደፊቱም በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል መሆኑን ያሳውቃል፡፡

ይህ ልዩ ትኩረት የተሰጠው “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻን በማልማት ቱሪዝምን ከማስፋፋት እና ገጽታን ከመገንባት ባሻገር ለነዋሪዎቿ ምቹ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ማኔጅመንቱና መላው ሠራተኛ በማመናቸው ነው ድጋፉን ያደረጉት።

ስለሆነም “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ዓላማ ባንኩ ተቋማዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ቀደም ሲል እየሰራባቸው ካሉ ዘርፎች ጋር የሚጣጣም በመሆኑ የዚህ ፕሮጀክት አጋር በመሆኑ ደስታቸው የላቀ መሆኑንም ነው በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት አባላት የገለፁት።

ባንኩ ወደፊትም የኢትዮጵያን ገጽታ በማስዋብና በማሻሻል ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ መሰል ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ አገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ የስራ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

Categories: Uncategorized