የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 (2023/24) በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 (2024/25) በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ የሚያካሂድበትን ዓመታዊ ጉባኤ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋናው መሥሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ጉባኤው በባንካችን ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ መልእክት ነው የተጀመረው፡፡ አቶ አቤ በመክፈቻ መልዕክታቸው እንደተናገሩት ባንካችን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአንድ ድርጅት የሥራ አፈፃፀም ዋነኛ መለኪያ በሆነው ትርፋማነት ያስመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በአብዛኛዎቹ ሌሎች የሥራ አፈፃፀም መለኪያዎችም እንዲሁ አበረታች አፈፃፀም ማስመዝገቡን የገለፁት አቶ አቤ ሀብት ማሰባሰብ፣ ትርፋማነት እንዲሁም የባንኩን የገበያ ድርሻ ማስጠበቅ እና ማሳደግ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ዋነኛ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ አቤ በመክፈቻ መልእክታቸው በርካታ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ እና ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ባንኩ የጀመረው የለውጥ ሥራን በአግባቡ መተግበር እና ውጤታማ ማድረግ፣ የደንበኛ አያያዝ እና ግንኙነትን ማሻሻል እንዲሁም ዲጂታል የባንክ አገልግሎት አጠቃቀምን ማሳደግ ሌሎች ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ አቤ አመልክተዋል፡፡ በጉባኤው የኮርፖሬት፣ የሪጅኖች፣ ዲስትሪክቶች እና በተወሰነ ደረጃ የቅርንጫፎች አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚቀርብ የገለፁት አቶ አቤ፣ በመልካም አፈፃፀም ተሞክሮዎች፣ በትኩረት አቅጣጫዎች፣ ሊሻሻሉ በሚገቡ ጉዳዮች እና በሌሎችም ላይ ጉባኤው የሚወያይ ይሆናል ብለዋል፡፡ ጉባኤው እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል፡፡