የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እና የዋና መ/ቤት ሕንፃ ምርቃት የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡ • ይህ የተገለፀው በአዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ 48ኛ ፎቅ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እና የዋና መ/ቤት ሕንፃ ምርቃት የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡ • ይህ የተገለፀው በአዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ 48ኛ ፎቅ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ======== የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም አዲሱን የዋና መ/ቤት ህንፃ ምርቃት በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡ ሁነቱን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንዳሉት ባንኩ ኢትዮጵያንም ሆነ ባንኩን በአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚያስነሱ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን ሰማይ ጠቀስ ህንፃ በ80ኛ ዓመቱ ላይ እውን አድርጓል፡፡ የዚህ ስኬት መሠረት የሆኑትና በባንኩ ላይ እምነት አሳድረው አብረው የዘለቁት መላ ኢትዮጵያውያን እና የባንኩ ደንበኞች ክብር እንደሚገባቸው የገለጹት አቶ አቤ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1942 በ1 ሚሊዮን የማሪያትሬዛ ካፒታል ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ 824 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ፣ 1.1 ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት፣ ከ1,800 በላይ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት አቶ አቤ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ለህብረተሰቡ የባንክ አገልግሎትን በማዳረስ፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ በሀገራችን የሚከናወኑ በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ሁሌም በቀዳሚነት 80 ወርቃማ አመታትን ማሳለፉንም ነው አቶ አቤ የተናገሩት፡፡ ባንኩ በ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ላይ የሚያስመርቀው የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ የባንኩን ዘመናዊ አገልግሎት ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግና አዲስ አበባ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ደረጃ የሚመጥን የዋና መ/ቤት ህንፃ ለመገንባት የነበረውን የረጅም ጊዜ ውጥን እውን የተደረገበት መሆኑን አቶ አቤ ገልፀዋል:: ባለ53 ወለል የሆነው ህንፃ በርዝመቱ ከአፍሪካ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች አንዱና በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው መሆኑን ነው አቶ አቤ ያስረዱት፡፡ ለባንኩ የአሁን ደረጃና ርዕይ የሚመጥን የዋና መ/ቤት ህንፃ አግኝተናል ያሉት አቶ አቤ ከዚህ በተጨማሪም በህንፃው መገንባት አዲስ አበባ ለከተማ ውበት እና ለቱሪስት መስህብ የሚሆን መዳረሻ ባለቤት ሆናለች በማለት ገልፀዋል፡፡ የህንፃው ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኘና የግንባታው አጠቃላይ ሂደትም በአይነቱ አዲስ የሆነ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተደረገበት መሆኑንም ነው አቶ አቤ ጨምረው የገለጹት፡፡ ተጨማሪ ያንብቡ፡ https://combanketh.et/.../press_Release_H_Onewbuilding...