የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሥራ አመራር አባላት በኬኒያ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ በታለመው በዚህ የልምድ ልውውጥ ላይ በአቶ አቤ ሳኖ የሚመራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ አመራር አባላት ልኡክ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያላቸውን አቅም በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሻል ብሎም ለኢትዮጵያ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነት አጀንዳ ስኬት በጋራ አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቲጂካዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያው ቀን የሥራ ጉብኝት ልኡኩ ከኬሲቢ ግሩፕ (KCB’s Group) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ፖል ሩሶ ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኬኒያ ውስጥ ከኤም-ፔሳ (M-PESA) ጋር በጋራ በመሥራት የደንበኞቻቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ በርካታ አገልግሎቶችን ማቅረብ ያስቻላቸውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡ ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣው ልኡክ በቀጣይ ከሳፋሪኮም ኃ.የተ.የግ.ኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ፒተር ንዴግዋ ጋር ፍሬያማ ውይይት ያካሄደ ሲሆን፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሊጠቀምበት ስለሚገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ ሰፊ የገበያ እድል መክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ወስጥ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ያለ መሆኑን አንስተው፣ በተለይ ገጠራማ አካባቢዎችን ጨምሮ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡