የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሶስት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የክብር ሽኝት አደረገ፡፡ • ባንኩን ለተቀላቀሉ ለሶስት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም አቀባበል አድርጓል፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በአባልነት ሲያገለገሉ የቆዩት አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ፣ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና አቶ ነብዩ ሳሙኤል የአገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው የክብር ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡ በዕለቱ ተሰናባች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ለተኩት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፣ ወ/ሮ ትዕግስት ሀሚድ እና አቶ ወንድምአገኘው ነገራ እንዲሁ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኘሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ተሰናባች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላቱ በባንኩ በሃብት አሰባሰብ፣ በተደራሽነትና ባለፉት አመታት በአጠቃላይ ለተገኘው አፈፃፀም እና ለተሰሩት መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ስራዎች የአመራር ሚናቸው የላቀ ነበርና እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ ተሰናባች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባላትም በበኩላቸው ባንኩ የሃገራችን ቁልፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የግዙፍ ሃገራዊ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም አጋዥ መሆኑን በቆይታቸው በተግባር መረዳታቸውን ጠቅሰው ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ አዲስ ተተኪ የቦርድ አባላትም በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚና ግዙፍ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባል በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ ባንኩ የጀመራቸውን ሁሉን አቀፍ የለውጥ ስራዎች ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የአገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው ለተሰናበቱት የቦርድ አባላት የማስታወሻ ስጦታና የምስጋና የምስክር ወረቀትም ተበርክቷል፡፡