የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያየ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ በፈቃዳቸው እንዲመልሱ ያሳስባል!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካጋጠመው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሰዱና ያልተገባ የገንዘብ እንቅስቃሴ ካከናወኑ ግለሰቦች መካከል ብዙዎች የተደረገላቸውን ጥሪ ኣክብረው የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች እየቀረቡ እየመለሱ በመሆኑ ከስህተታቸው የመመለስ በጎ ምላሽነቱን እናደንቃለን። እስካሁን ቀርበው ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችም እስከመጪው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የባንካችን ቅርንጫፍ በመቅረብ ተመላሽ እንዲያደርጉ ባንካችን የመጨረሻ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠቅመው አላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦች ላይ ደረጃ በደረጃና በተከታታይ የተለያዪ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚገደድ እንገልፃለን:: ከታቀዱት ዋና ዋና እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት እንዳሉ እንዲታወቁ ይፈለጋል:- 1. ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ሥም ዝርዝር በየቅርንጫፎች እና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት ኣካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎችን እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ እንገልጻለን፡፡ 2. ⁠ከዚህ በላይ በተጠቀሰው እርምጃ መሰረት አሁንም ቀርበው የማይመልሱ ከሆነ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በድርጊቱ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ፎቶግራፋቸውን እና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልፁ መረጃዎች ባንኩ በመረጠው የብዙሀን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ያሳስባል፡፡ 3. ⁠ከዚሁ በላይ ከተጠቀሱት እርምጃዎች ጎን ለጎንም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የወሰዱትን ገንዘብ እስከ ቅዳሜ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦችን ከፍትህ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣የፍትሐ ብሔርና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያደርግ ያሳስባል።