የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 50 ሚሊዮን ብር ለነጋድራስ የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች እንደሚያበድር ቃል ገባ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዘጋጅነት ነጋድራስ የሥራ ፈጠራ ውድድር ዛሬ ሲጠናቀቅ ለመጨራሻዎቹ 5 የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች ማበረታቻ እንዲሆን ለእያንዳንዳቸው 200 ሺ ብር አበርክቷል። የባንካችን ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በCBE studio በተደረገው የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት አገር የምትበለጽገው በዋናነት ሥራ በመፍጠር ከራሳቸው አልፈው የሌሎች ዜጎችን ሕይወት በሚቀይሩ ታታሪዎች ጥረት ስለሆነ፣ ተወዳዳሪዎች ሁሉ ያሳዩትን የሥራ ፈጠራ ተነሣሽነት አጠንክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የወደፊት ተስፋ ብሩህ ፈርጦችን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰተዋል። እንደ ነጋድራስ የመሳሰሉ የፈጠራ ሥራ ውድድር መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት ለአገር ግንባታ ግብአት የሚሆኑ ሐሳቦች ተፀንሰው ለትግበራ በሚበቁበት ዕቅድ መልክ እንዲወለዱ በማበረታታት ረገድ በመልካም ምሳሌነት እንደሚጠቀስ ተቁመው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንን የውድድር መርሃ ግብር አዘጋጅቶ እዚህ በማድረሱ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። አቶ አቤ ሳኖ በመጨረሻም ለፍፃሜ ለደረሱት ለአምስቱም ተወዳዳሪዎች ያለማስያዣ የሚሆን 50 ሚሊዮን ብር የመካከለኛ ዘመን ለስራ ማስኬጃ እና ለማሽነሪ መግዣ የሚሆን የባንክ ብድር በአነስተኛ የማበደሪያ ወለድ ለመስጠት ባንኩ መወሰኑን ነው በዕለቱ ለተወዳዳሪዎች ያበሰሩት። የነጋድራስ የሥራ ፈጠራ ውድድር የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣይ ይህ ውድድር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በመነጋገር በቀጣዩ አመት በኤክስክሉሲቭ ስፖንሰርነት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለፁት። በዚህ የነጋድራስ የምዕራፍ ሁለት የፍፃሜ ውድድር የነዳጅ መኪናን ወደ ኤሌክትሪክ መኪና የሚቀይር ፈጠራ ባለቤት የሆነው ዘመኑ ሲሳይ አሸናፊ ሆኗል፡