የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ያቀረበው ብድር የንግድ እንቅስቃሴውን ማሳለጡ ተገለፀ፡፡

መላው ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው የኦሎምፒክ ውድድር በፈረንሳይ ፓሪስ አዘጋጅነት ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ አትሌቶቻችን በዓለም መድረክ ላይ በተደጋጋሚ ሰንደቃችንን ከፍ አድርገው የሚሰቅሉበት የኦሎምፒክ ውድድር ለሀገራችን ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በዘንድሮው የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይህን በርካቶች በጉጉት የሚከታተሉት የኦሎምፒክ ውድድር ከመክፈቻው እስከመዝጊያው በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልዩ የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪዚዳንት ተወካይ እና የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ኢቢሲ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ልዩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትን በማስመልከት አዘጋጅቶት በነበረው ልዩ የቴሌቪዥን ዝግጅት የቀጥታ ስርጭት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡ አቶ ኤፍሬም በቀጥታ ስርጭቱ ላይ በቅርቡ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ የባንክ ሥራ አፈፃፀም መለኪያዎች ባንኩ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችን እና ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ባንኩ ሲያካሂድ የነበረው መጠነ ሰፊ ተቋማዊ ለውጥ ለተመዘገበው ውጤት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አቶ ኤፍሬም አመልክተዋል፡፡ ባንኩ እያካሄደ የሚገኘው ደንበኛ ተኮር ተቋማዊ ለውጥ ከአደረጃጀት ጀምሮ ለደንበኞች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል እና ለደንበኞች ምቹ የሆኑ አዳዲስ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል መሆኑን ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት፡፡ ያለፈው በጀት ዓመት የተሻለ አገልግሎት መስጠት የተቻለበት እና የተቋማዊ ለውጡ ፍሬ የታየበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ ባንኩ ከፍተኛ የሆነ ገቢ እና ትርፍ ያገኘበት እንዲሁም ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበበት ዓመት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም የባንኩ የብድር ማስመለሰ ሥራም ውጤታማ እንደነበር ገልፀው፣ ከ218 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ብድር መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡ ባንኩ ባለፈው ዓመት ከሰጠው ብድር ውስጥ ከባለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ አብዛኛው ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰጠ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ገልፀው፣ ይህም ሀገሪቷ ውስጥ የሚታየው በርካታ የንግድ እንቅስቃሴ የበለጠ እንዲሳለጥ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የተሻለ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም ቴክኖሎጂ ላይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም በቀጥታ ስርጭቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ የባንክ አገልግሎት ዲጂታላይዝድ ወደሆነ አሠራር እያመራ ነው ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ ለዚህም ባንኩ ባለፉት ዓመታት የቴክኖሎጂ መሰረት ልማት ላይ እና ደህንነት ላይ ትልቅ ሥራ በመሥራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በባንኩ ከተካሄደ 32 ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ 72 ከመቶ የሚሆነው በባንኩ ዲጂታል የአገልግሎት አማራጮች መፈፀሙን አቶ አፍሬም ገልፀዋል፡፡ ይህም ባንኩ በሀገራችን በዲጂታል የባንክ አገልግሎት መስክ ያለውን ጉልህ ድርሻ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም በዚሁ ዝግጅት ላይ ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚሰራቸው ተግባራት አንዱ የስፖርቱን ዘርፍ መደገፍ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህ ረገድ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የስፖርት ማህበር በማቋቋም ትልቅ አስተዋትጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፓሪስ 2024 ኦሎምፒከ የሚወዳደሩ አትሌቶችን ማስመረጥ መቻሉ፣ በኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን መሆኑ እንዲሁም ለ7ኛ ጊዜ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ የተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ልዩ የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር በመሆን የሀገራችን ህዝቦች ውድድሮችን በቀጥታ እንዲመለከቱ በማስቻሉ የተሰማውን ደስታ እየገለፀ፣ ለአትሌቶቻችን መልካም እድል ይመኛል፡፡