የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የገንዘብ ድጋፉን በመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት አስረክበዋል፡፡ አቶ አቤ ማእከሉ ከ7 ሺ 500 በላይ የሀገር ባለውለታ አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት አንስቶ መጠለያ በመስጠት እና በመንከባከብ እየሠራ ያለው ሥራ ሊመሰገን እና ሊደገፍ የሚገባው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማእከሉ ለሚያከናውነው የበጎ ተግባር ሥራ ያለበትን ከፍተኛ ወጪ እንዲሁም አገልግሎቱን ለማስፋት በማስገንባት ላይ ያለውን ባለ 15 ወለል ህንፃ ግንባታ ወጪ ታሳቢ በማድረግ ባንኩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የገንዘብ ድጋፉ መደረጉን አቶ አቤ ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለማዕከሉ ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ አቤ፣ ወደፊትም ከማእከሉ ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጤናው ዘርፍ ߹ በትምህርት߹ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በሰብአዊ ሥራ ድጋፍ እና በሌሎችም ዘርፎች ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለፉት አምስት ዓመታት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡