ባንኩ የእውቅና እና የምስጋና መርሀ-ግብር አካሂዷል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመወከል በሀገራዊ፣ አህጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረክ በተከናወኑ ስፖርታዊ ሻምፒዮኖች ላይ በመሳተፍ የላቀ ስኬት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች፣ የስፖርት ባለሙያዎች እና አመራሮች የእውቅና እና የምስጋና መርሀ-ግብር ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ያገኛቸውን ከ40 በላይ ዋንጫዎች ለባንኩ ባስረከበበት በዚህ መርሀ ግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት እና የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ የስፖርት ማኅበሩ በተሳተፈባቸው የተለያዩ ሀገራዊ እና አህጉራዊ የስፖርት ውድድሮች ስኬታማ ዓመት ማሳለፍ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካው የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ፣ ለ7 ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ የሴቶች ቡድን በሴካፋ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ መሆኑና ኢትዮጵያን በመወከል በፓሪስ ኦሎምፒክ 2024 የተሳተፈችው የባንኩ አትሌት ፅጌ ዱጉማ የብር ሜዳሊያ ማምጣት መቻሏ አመቱን ልዩ እንደሚያደርገው አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ጨምሮ የስፖርት ማኅበሩ ላስመዘገበው ስኬት በየበኩላቸው አስተዋፅኦ ላበረከቱት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ በተሳተፈባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ለተገኘው አኩሪ ድል የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፈዋል፡፡ ዘንድሮ የፕሪሚየር ሊጉን እና የሴካፋ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካው የባንኩ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በተከታታይ ባስመዘገባቸው ድሎች ባንኩ የስፖርቱ ዘርፍ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ማስቻሉን የገለፁት አቶ አቤ፣ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ አቤ ባንኩ ባለፈው ዓመት በስፖርቱ ዘርፍ ያስመዘገበው ውጤት የሚያኮራ መሆኑን ገልፀው፣ ተግተው በመሥራት ባንኩ የሚጠብቀውን ውጤት ማምጣት ለቻሉት ስፖርተኞች እና አሰልጣኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የተገኘው ውጤት የሁሉም ተሳትፎ ድምር ውጤት ነው ያሉት አቶ አቤ፣ በዚህ ሂደት በየደረጃው ለተሳተፉ አካላት፣ ለደጋፊዎች፣ ለሚዲያ አባላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ አቤ በቀጣይ የተገኘውን ውጤት ማስጠበቅ እና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልፀው፣ ስፖርተኞች በየደረሱበት የባንኩ አምባሳደር በመሆን ባንኩን በሚገባ እንዲያስተዋውቁ አደራ ብለዋል፡፡ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ መስፍን ቸርነት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉጊዜ ግንባር ቀደም መሆኑን ገልፀው፣ በስፖርቱ ዘርፍም ሀገርን በዓለም መድረክ የሚወክሉ ስፖርተኞችን በማፍራት እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ መንግስት ከባንኩ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ሌሎች የቡድኑን አባላት ጨምሮ በዓመቱ በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ባንኩንና ሀገራቸውን ወክለው የተሳተፉ እና ስኬታማ የሆኑ ስፖርተኞች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ መስፍን ቸርነት እጅ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው የምስጋና መርሀ ግብር ስፖርት ማኅበሩ በዓመቱ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን እና የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያን ጨምሮ ሌሎች አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።