በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2017 በተደረገው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የቪዛ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ቻድ ፖሎክ ስምምነቱን ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የቪዛ ኢንተርናሽናል ስትራቴጂክ ስምምነት መንግስት ባደረገው የፋይናንሺያል ፖሊሲ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን ለመፈጸም ወሳኝ ነው፡፡ የባንኩን አሠራር ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የቪዛ ኢንተርናሽናል ም/ፕሬዚዳንት እና የምስራቅ አፍሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቻድ ፖሎክ በበኩላቸው ከኢ.ን.ባ ባለው አጋርነት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ቪዛ ከኢ.ን.ባ ጋር ያለው አጋርነት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚኖር የገንዘብ እንቅስቃሴ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡ ቪዛ ኢንተርናሽናል እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ስምምነት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ ቪዛ ካርድን በብዛት ለ ኢ.ን.ባ ደንበኞች ለማቅረብ እና ለባንኩ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት እንደሚያስችል ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ደንበኞቹ እንዲገለገሉበት ያስተዋወቀ ተቋም ነው፡፡ ከፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አበልጻጊዎች ጋር አብሮ በመሥራትም የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ለደንበኞች ምቹ እና ቀልጣፋ እንዲሆን አድርጎል፡፡ የ2017 ዓ/ም የዓዲስ ዓመት ልዩ ፕሮግራም ከፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አበልጻጊ ድርጅቶች ጋር ቆይታ አድርጎ የሥራቸውን እንቅስቃሴ አስተዋውቋል፡፡