በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስትራቴጂክ አጋርነት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅነት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረው ሶስተኛው የሳይበር ደህንነት ወር መርሃ ግብር ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር መክፈቻ መርኃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ተከናውኗል። የሳይበር ደህንነት መጠበቅና መረጋገጥ ከፋይናንስ ተቋም ጋር ያለውን ከፍተኛ እና ቀጥተኛ ቁርኝት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንዲሁም፣ አጠቃላይ ለሀገራችን ሉአላዊነት መረጋገጥ ያለውን ትልቅ ድርሻ በመገንዘብ ባንኩ የመርሀ ግብሩ ስትራቴጂክ ስፖንሰር ሊሆን መቻሉ ታውቋል፡፡ በስካይ ላይት ሆቴል በተከፈተው ኤግዚቢሽን እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በሚካሄዱ የተለያዩ ኮንፍራንሶች በወሩ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ለማህበረሰቡ እና ለተቋማት ግንዛቤ ለመፍጠር ይሰራል፡፡ በተጨማሪም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነታቸዉን እንዲለዩና እንዲቀንሱ፣ የግሉ ዘርፍ በሳይበር ደህንነት ያለዉን ሚና እና አበርክቶ ከፍ እንዲያደርግ እና የሳይበር ደህንነት ጉዳይ እንደ ወሳኝ ጉዳይ እንዲወሰድ የማስገንዘብና የማበረታታት ስራዎች እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ "የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለሃገር ሉአላዊነት" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል፡፡