በሃገራችን ሁለንተናዊ የልማት እና የዕድገት ጉዞ ውስጥ ቀዳሚ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በአጋርነት፤ ዜጎች ዲጂታል የብድር እና የቁጠባ አገልግሎቶችን በቴሌብር እንዲያገኙ የሚያስችል የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀ መርሐ-ግብር በይፋ አስጀምረዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት በአጋርነት ያስጀመሩት አገልግሎት የባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋግጥ የሚያስችል፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣን እና ቀላል በሆነ አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ከ80 ዓመታት በላይ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ኢንዱስትሪውን በመምራት ላይ የሚገኘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው ጥቅም ላይ በማዋል የደንበኞቹን ፍላጎት እና እርካታ ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት በአሁኑ ጊዜ ከ38 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የተቀማጭ ገንዘቡን ከ 1.1 ትሪሊየን ብር በላይ ማሻገሩ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለያዩ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የኢትዮጵያን ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር በበላይነት እየመራ የሚገኝ ሲሆን፣ በሀገራችን የፋይናንስ አካታችነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ የሆነውና ላለፉት 129 ዓመታት በሃገራችን የቴሌኮም አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ የመሆን ራዕዩ አካል የሆነውን ቴሌብር የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ባስጀመረ በ2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ34.05 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እና የዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ጊዜው የዲጂታል መሆኑን ገልፀው፣ ባንኩ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆኑን አስገንዘበዋል፡፡ አቶ አቤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ ለመሥራት ያሠሩት ውል ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይ. ፍሬሂወት ታምሩ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ከአንጋፋው ተቋም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጥምረት መሥራቱ ሕብረተሰቡ አሁን ከሚያገኛቸው አገልግሎቶች የተሻለ እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል። በዕለቱ በይፋ በተጀመረው በዚህ አገልግሎት ግለሰቦች፣ በንግድ ስራ የተሰማሩ ተቋማት እንዲሁም ህጋዊ ወኪሎች የአነስተኛ ቁጠባ እና የብድር አገልግሎቶችን በቴሌብር ማግኘት እንደሚችሉ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡ የግለሰብ ደንበኞች እና ተቋማት በቴሌብር የሚያከናውኗቸውን ግብይቶች መሰረት አድርጎ በሚሰራ የብድር ቀመር ስሌት፣ እንዲሁም በቴሌብር የደሞዝ ተከፋይ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ያለ ማስያዥያ በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ የብድር አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ የሚሰጥ አገልግሎት በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ደንበኞች ተያዥ ሳያስፈልጋቸው ያለዋስትና የቴሌብር እና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ የብድር አገልግሎት ማግኘት ማስቻሉ ልዩ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡ ደንበኞች የተበደሩትን ብድር በወቅቱ በመመለስና የተለያዩ ግብይቶችን በቴሌብር በመፈጸም መበደር የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ማሳደግ እንደሚችሉም ነው የተገለፀው፡፡