የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 622.9 ሚሊዮን ብር (78 በመቶ) ማስመለስ መቻሉን ገለጸ፡፡

ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ መጋቢት 6፣ 2016 ዓ.ም ሌሊት በተፈጠረ ችግር ምክንያት 801,417,747.81 ብር ያላግባብ ተወስዶ እንደነበር ባንኩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያሳወቀ ሲሆን፣ 622.9 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ከባንኩ አላግባብ የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለሰ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ በተዘጋጀው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለፁት ችግሩ በተከሰተበት ቀን ከምሽቱ 3፡38 ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 8፡45 ድረስ በ25,761 ሂሳቦች አማካኝነት 238‚293 ህገወጥ ግብይቶች ተከናውነዋል፡፡ አቶ አቤ ችግሩ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ የባንኩን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለተወሰኑ ሰዓታት በማቆም እና ችግሩ በተከሰተበት ሰዓት በገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ ሂሳቦችን በማገድ የጉዳት መጠኑን መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ አቶ አቤ እንዳሉት ባንኩ በቀጣይ በወሰዳቸው እርምጃዎች ያላግባብ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከተደረገባቸው እና በቂ ገንዘብ ከነበራቸው ከ10,727 ሂሳቦች ቀጥታ ብር 44,668,232.41 ተመላሽ የተደረገ ሲሆን፣ ከ15,008 ሂሳቦች ደግሞ በከፊል ማለትም ብር 205,805,340.9 ብር ተመላሽ ተደርጓል፡፡ በጉዳዩ ተሳትፎ የነበራቸው 9,281 ያህል ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ ብር 223,475,369.31 ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት የመለሱ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አቤ፣ 5,160 ደንበኞች ደግሞ በከፊል ማለትም ብር 149,021,191.37 መመለሰቻውን አሳውቀዋል፡፡ አላግባብ ከወሰዱት ብር 9,838,329.12 እስካሁን ምንም ያልመለሱ 567 ግለሰቦች መኖራቸውንም ነው አቶ አቤ የገለፁት፡፡ አቶ አቤ ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ በፈቃደኝነት የማይመልሱ ግለሰቦችን በተመለከተ ቀደም ሲል ባንኩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አስፈላጊውን ተግባራት በቅደም ተከተል በማከናወን ጉዳዩ ለህግ አካል እንደሚቀርብ ገልፀዋል፡፡