የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያላግባብ ተወስዶ ያልተመለሰውን ቀሪ ገንዘብ ለማስመለሰ ወደቀጣይ እርምጃዎች እንደሚገባ ገለፀ፡፡

በዛሬው እለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለፁት ባንኩ መጋቢት 6፣ 2016 ዓ.ም ሌሊት በተፈጠረ ችግር ምክንያት አላግባብ ከተወሰደበት 801,417,747.81 ብር ውስጥ 622.9 ሚሊዮን ብር (78 በመቶ) እስካሁን የተመለሰ ሲሆን ብር 168,609,283.7 ለመመለስ ቃል ተገብቷል፡፡ አቶ አቤ አላግባብ በ567 ግለሰቦች የተወሰደውን ቀሪ ብር 9,838,329.12 ለማስመለሰ ባንኩ ወደቀጣይ እርምጃዎች እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ገንዘቡን ያልመለሱት ግለሰቦች እንደሚታወቁ የገለፁት አቶ አቤ ከተወሰደው ገንዘብ ውስጥ አንድ ግለሰብ የወሰደው ከፍተኛው ብር 304 ሺህ ብር ሲሆን ከአምስት ብር በታች የወሰዱም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ አቤ ባንኩ በቀጣይ ገንዘቡን የወሰዱትን ግለሰቦች የስም ዝርዝር ሂሳባቸው ባለበት ዲስትሪክት እና ቅርንጫፍ እንዲሁም በባንኩ ማኅበራዊ ሚዲያ በመለጠፍ እስከ ፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ እንዲመልሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እስከተጠቀሰው ቀን ድረስ ገንዘቡን በማይመልሱ ግለሰቦች ላይ ጉዳዩን እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የመውሰድ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ አቤ ገልፀዋል፡፡