በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡

ይህ የተገለፀው መጋቢት 16፣ 2016 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ለተገኘው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩ የ2023/24 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ነው፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ እንዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሀገር የልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ያለ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የሚጠብቀበትን እየተወጣ እንዲቀጥል እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ደግሞ የባለድርሻ አካላት የፖሊሲን ጨምሮ ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርጉለት እንደሚገባ ዋና ሰብሳቢው አሳስበው፣ ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ ባንኩ በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ የሠራው ሥራ የሚያስመሰግነው እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበትንም መንገድ ዋና ሰብሳቢው አድንቀዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የባንኩን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ላነሷቸው ጥያቄዎች የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ጨምሮ የሚመለከታቸው የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ መስጠታቸው እና የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት የሚሠራውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመረጃ ደህንነት ሥርዓት ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡