የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ የተወሰደበትን ገንዘብ በማስመለስ ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሠራተኞች፣ ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች እውቅናና ሽልማት ሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጠረ ችግር ምክንያት ያለአግባብ ተወስዶ የነበረውን ገንዘብ በማስመለስ ሂደት የላቀ ሙያዊ እገዛ ላደረጉ ሠራተኞች እና የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች እውቅናና ሽልማት በባንኩ ዓመታዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ተሰጥቷል፡፡ የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ቀን በትጋት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ሰባት የባንኩ ሠራተኞች ከባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እጅ የምስክር ወረቀት እና ሽልማት ተቀበለዋል፡፡ ገንዘቡን በማስመለሰ ሂደት አዳማ፣ ጅማ እና ደብረ ማርቆስ በቅደም ተከተላቸው ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ዲስትሪክቶች በመሆን የምስክር ወረቀት እና ሽልማት ወስደዋል፡፡ ከተወሰደባቸው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በማስመለስ አዳማ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ አሰላ እና ደብረ ብርሀን ዲስትሪክቶች በቅደም ተከተላቸው ከአንድ እስከ አምስት በመውጣት የምስክር ወረቀት እና ሽልማት የወሰዱ ዲስትሪክቶች ናቸው፡፡ የተወሰደባቸውን ገንዘብ በማስመለስ ረገድ የላቀ አፈጻፀም በማስመዝገብ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንድ እስከ አስር የወጡት እና የምስክር ወረቀት እና ሽልማት የወሰዱት ቅርንጫፎች አዳማ ቅርንጫፍ፣ ነጭ ሳር ቅርንጫፍ፣ ቅሊንጦ ቅርንጫፍ፣ ሀረማያ ቅርንጫፍ፣ ሰቀቀሎ ቅርንጫፍ፣ ገንደጋራ ቅርንጫፍ፣ አዳማ ዋናው ቅርንጫፍ፣ ፉራ ቅርንጫፍ፣ ሽምብጥ ቅርንጫፍ እና ጋሮ ቅርንጫፍ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጠረ ችግር ምክንያት ያለአግባብ ከተወሰደበት ብር 801.4 ሚሊዮን ገንዘብ ውስጥ 99.5 በመቶው የተመለሰ መሆኑ በሽልማት ሥነ -ሥረዓቱ ላይ የተገለፀ ሲሆን ቀሪውን ገንዘብ የማስመለሥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡ ለተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ እንላለን!