የአቶ አቤ ምስጋና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 (2023/24) በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 (2024/25) በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ ዓመታዊ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ምስጋና ለሚገባቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጠረ ችግር ምክንያት ያለአግባብ ተወስዶ የነበረውን ገንዘብ በማስመለስ ሂደት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የባንኩ ሠራተኞች፣ ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች፣ የመንግስት አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ባንኩ ያለአግባባ የተወሰደበትን ገንዘብ ለማስመለሰ የሠራውን ስኬታማ ተግባር እውቅና ለሰጡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አቶ አቤ ሳኖ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እና ሽልማት ለወሰዱ ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች ከአቶ አቤ የእንኳን ደስ አላችሁ መልካም ምኞት መግለጫ እና ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡ ባንኩን በተለያዩ ስፖርቶች በመወከል ውጤታማ ለነበሩ እና የባንካችንን ስም ላስጠሩ የባንኩ ስፖርተኞች ፣ የቡድን አባላት እና አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል አቶ አቤ፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ለተሻለ ለውጥ እና ውጤት እንዲተጉ የማነሳሳት ሚናቸውን እየተወጡ ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሠረታው የሠራተኞች ማኅበር መሪዎች በአቶ አቤ ተመስግነዋል፡፡ በመጨረሻም በባንካችን ሥራ ላይ ትልቅ እንቅፋት የፈጠሩ ሁኔታዎችን በመቀልበስ የተለያዩ ውሳኔዎችን ላስተላለፉ የመንግስት አካላት ከአቶ አቤ ሳኖ ምስጋና ቀርቧል፡፡