አቶ አቤ ሳኖ የ2016 ዓ.ም የአቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት የዳይመንድ ደረጃ ኒሻን እና ልዩ ዋንጫ ተረከቡ፡፡

ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን ላበረከቱ ተቋማት እና አመራሮች ሽልማት የሚያበረክተው አቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት ሥነ - ሥርዓት ሐምሌ 14 ቀን 2016 በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ተከናውኗል፡፡ በሥነ - ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፕሬዚዳንቱ አቶ አቤ ሳኖ ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ባንኩ ከ75 ዓመታት በላይ አገርን በማገልገልና በተከታታይ ትርፋማና ስኬታማ በመሆኑ የዳይመንድ ደረጃ ልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ እንዲሁም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለባንኩ ትርፋማነትና ስኬታማነት ባሳዩት ብቃት ያለው አመራር የ2016 ዓ.ም. የዳይመንድ ደረጃ ኒሻን እና ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሽልማት ሥነ- ስርዓቱ ላይ በመገኘት ዕውቅናውንና ሽልማቱን የተረከቡት የባንኩ የሰው ኃይል ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እና ሌሎችም የባንኩ ኃላፊዎች ዛሬ በፕሬዚዳንቱ ቢሮ በመገኘት ሽልማቱን ለአቶ አቤ ሳኖ አስረክበዋቸዋል፡፡ ''እንኳን ደስ አሎት'' በማለትም ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ ባጠናቀቅነው በጀት ዓመት በታሪኩ 'ከፍተኛ ነው' የተባለውን ትርፍ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡