የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሠራተኞች የስፖርት ውድድር የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አቤ ሳኖ ገለጹ።
ከግንቦት 2016 ዓ/ም ጀምሮ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያው የሚገኙ የባንኩ ዲስትሪክቶች መካከል ሲካሄድ የቆየው የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ ተጠናቋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደውን የፍፃሜ ጨዋታ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደተናገሩት የአካል ብቃትን ለመጠበቅና በሠራተኞች መካከል ያለውን መቀራረብ ለማጠናከር መሰረት ያደረገው ስፖርታዊ ውድድር የበለጠ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። ባንካችን በሚሳተፍባቸው ዘርፎች ሁሉ ቀዳሚ መሆን ይገባዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከሰሞኑ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር በባንኩ የሴቶችና የወንዶች እግር ኳስ ቡድኖች የተመዘገቡ ውጤቶች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው ብለዋል። በሠራተኞች በኩል በዋናው መ/ቤት እና በመገናኛ ዲስትሪክት መካከል ለዋንጫ በተደረገ ግጥሚያ የዋና መስሪያ ቤት ሠራተኞች ቡድን የመገናኛ ዲስትሪክትን 3 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫ አንስቷል። በሥራ መሪዎች በኩል የዋናው መ/ቤት የሥራ መሪዎች ከቂርቆስና መርካቶ ዲስትሪክት ጥምረት ጋር ተጋጥመው ፤ የዋና መስሪያ ቤት የሥራ መሪዎች ቡድን በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫ አንስቷል።