የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚያካሂደው 3ኛው የሳይበር ክህሎት የክረምት ፕሮግራም ዛሬ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የፋይናንስ ሥርዓት ወደ ዲጂታል እየተሸጋገረ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ባንኮችም ከጊዜው ጋር መዘመን አለባቸው ብለዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋሞቻችን በውጭ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለማስቀረት የታዳጊ ወጣቶችን የሳይበር ክህሎት በትብብር ማበልፀግ እንደሚገባም ወ/ሮ ትዕግስት ተናግዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከስተመር ኤክስፔሪያንስ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኃየለእየሱስ በቀለ በተለያዩ ዘርፎች ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሀገር ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የፈጠራ ሥራዎችንም በፋይናንስ ይደግፋል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ዋና ተልዕኮ የሆነውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርፀት ሥራ በአግባቡ እንዲያከናውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ስለሚያደርገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ በሳይበር ታለንት የክረምት ፕሮግራም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር 60፣ በሁለተኛው ዙር 120 ታዳጊ ወጣቶች የሰለጠኑ ሲሆን በ3ኛው ዙር 300 ታዳጊ ወጣቶችን መቀበሉን በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡