የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀይብሪድ ዲዛይን ኅ.የተ.የግ.ማ (ራይድ ትራንስፖርት) በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ በሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ባንኩን በመወከል ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገብረማሪያም እንደተናገሩት የራይድ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ደንበኞችን በባንኩ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ክፍያቸውን መፈፀም ለማስቻል፣ ራይድ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በጋራ ለመሥራት፣ ለኤሌክትሪክ መኪኖች ግዥ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ እንዲሁም በቀጣይ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ነው፡፡ አቶ ወጋየሁ ራይድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በደንበኝነት ለረጅም ጊዜ መሥራቱን ገልፀው፣ ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን እያቀረበ እና እያደገ ከሚገኘው ከዚህ ድርጅት ጋር መሥራት መቻሉ ሁለቱንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመግለፅ በቀጣይ በሌሎች ዘርፎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ የሃይብሪድ ዲዛይን ኅ.የተ.የግ.ማ (ራይድ ትራንስፖርት) የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ጌታቸው በበኩላቸው በርካታ ተሸከርካሪዎችን በመያዝ በትራንስፖርት ዘርፉ ጠንካራ ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኘው ራይድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደገረው የሥራ ስምምነት ትልቅ አንድምታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ አቶ ዘላለም ራይድ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ከሚሠራው ሥራ ጋር በተያያዘ ባንኩ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ግዥ ፋይናንስ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆኑ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው ስምምነት ከሁለቱም ተቋማት የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በርካታ የሚድያ አካላትም ተገኝተዋል፡፡