በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ በተመራው እና የዋናው መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና አካባቢው የሚገኙ የዲስትሪክት እና ቅርንጫፍ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዋናው መሥሪያ ቤት የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ውይይት፣ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ባደረገችበት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት በነበረው ሀገራዊ አፈፃፀም ላይ የተዘጋጀ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በቀረበው ሪፖርት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡ በወጪ ንግድ፣ በመንግስት ገቢ ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል። በአጠቃላይ በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከባለፈው በጀት ዓመት አንፃር የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት የተመዘገበበት እንደነበር ባሳየው በዚህ ሪፖርት፣ መስከረም 30፣ 2017 ላይ በሀገር ደረጃ አጠቃላይ የተቀመማጭ ገንዘብ መጠኑ 2.6 ትሪሊዮን መድረሱ ተመላክቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሀገር ደረጃ 121.5 ቢሊዮን ብር ብድር መለቀቁም ነው የተገለፀው፡፡ ሪፖርቱ ያመላከተው ሌላው ጉዳይ የዲጂታል ክፍያ አፈፃፀም ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን ነው፡፡ በሩብ ዓመቱ በሀገር ደረጃ አጠቃላይ 640 ሚሊዮን የገንዘብ ዝውውር በዲጂታል አማራጮች የተፈፀመ ሲሆን፣ ይህ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ438.4 ሚሊዮን አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ46 በመቶ እድገት ማሳየቱ ታይቷል፡፡ በገንዘብ ደረጃ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች በነበረው ዝውውር በሀገር ደረጃ አጠቃላይ የ3.1 ትሪሊዮን ብር ግብይት መፈፀሙን እና ይህም ከዓምናው የ2 ትሪሊዮን ብር አፈፃፀም 55 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በዚህ ምክንያት የተመዘገበው የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም በተለይ ከባንኩ ሥራ አንፃር ባለው በጎ እድል ላይ ተሰብሳቢዎቹ ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ውይይት የባንኩ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ከዋና ዋና መለኪያዎች አንፃር የተዳሰሰ ሲሆን፣ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በብድር አለቃቀቅ እና አሰባሰብ እንዲሁም በትርፋማነት ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡