የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጫና የሚቀንስና ካፒታሉን ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል፡፡ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ በማብራሪያቸውም የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸውና የብድር ወለዱም በጣም ከፍ በማለቱ በባንኩ ላይ ጫና መፍጠሩን አብራርተው፤ ባንኩ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቋም በመሆኑ 900 ቢሊየን ብሩ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ሆኖ እንዲከፈል እና መነሻ ካፒታሉም ከፍ እንዲል ውሳኔ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግሮና ውይይት ተደርጎበት እንዲፀድቅም የተከበሩ ዶ/ር ተስፋዬ ጠይቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ የቀረበውን ሞሽን የደገፈ ሲሆን፤ በቀጣይ በልማት ድርጅቶች በኩል ያለው አሰራር እንዲፈተሽ በምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ሞሽኑን አስመልክቶ ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች የገንዘብ ሚንስትሩ ክቡር እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የልማት ባንኮች እና የልማት ድርጅቶች ምን አይነት ኪሳራ ላይ ወድቀው እንደነበር የተከበረው ምክር ቤት ያውቀዋል ያሉት ክቡር ሚንስትሩ፤ መንግስት ‹‹ከዕዳ ወደ ምንዳ›› የሚለውን መሪ ቃል መሰረት አድርጎ በሰራው ማሻሻያ በርካታ የልማት ድርጅቶች ከኪሰራ ወደ ትርፋማነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም በልማት ድርጅቶች ላይ የተሻለ ቁጥጥርና ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ በመንግስት ላይ የተወሰነ ጫና የሚያመጣ ቢሆንም ሊደርስ ከሚችለው ከፍተኛ ጉዳት ግን የታደገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1346/2017 ሆኖ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል፡፡ ምንጭ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት