የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘የመረጃ ደህንነትን በመተባበር እናፀናለን’ በሚል ርእሰ ጉዳይ የፓናል ውይይት አካሄደ።

የሳይበር ደህንነት ወርን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2017 በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ‘የመረጃ ደህንነትን በመተባበር እናፀናለን’ በሚል ርእሰ ጉዳይ የፓናል ውይይት አካሂዷል። የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት የሚያስፍልገው እንደሆነ ገልፀው፣ ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ለመምከር የውይይት መድረኩን ማዘጋጀቱን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ በባንኩ ዓለም አቀፍ መስፈርትን መሰረት ያደረገ የመረጃ ደህንነት ሥርዓት መዘርጋቱን አመልክተዋል ። አቶ አቤ ባንኩ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም ከመሆኑ አንፃር ለጥቃት ተጋላጭነቱ ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀው፣ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብረው እየመጡ ያሉትን የዉጭ ጥቃቶች ለመመከት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባበሪ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ደህነት ወርን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ማክበሩን አድንቀዋል፡፡ የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር ‘የቁልፍ መሰረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉአላዊነት’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑን አቶ ዮዳሄ ገልፀው፣ የፋይናንስ ተቋማት በዲጂታል መሰረተ ልማታቸው ከፍተኛ የጥቃት ተጋላጭነት ስላለባችው ደህንነትን የማጽናት አቅምን መገንባት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። አቶ ዮዳሄ ድንበር የለሹን ተለዋዋጭና ውስብስብ የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ገልፀው፣ በዚህ አመት ተሻሽሎ የወጣውን የሳይበር ፖሊሲ በአግባቡ መተግበር እና በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል ። ‘የመረጃ ደህንነትን በመተባበር እናፀናለን’ በሚል ርእሰ ጉዳይ የተዘጋጀውን የፓናል ውይይት መነሻ ፅሁፍ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ዳይሬክተር አቶ ስዩም ዳምጠው አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። ዓለም አቀፉ የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም ለ21 ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን፣ በባንኩ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የመንግስት እና የባንኩን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።