ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በባንካችን ዋና መ/ቤት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ጌትነት ታደሰ በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ሦስተኛው ምዕራፍ 'ነጋድራስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ፈጠራ ውድድር' በሚል ተሰይሟል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች ሃሳቦቻቸውንና የስራዎቻቸውን ዝርዝር በእውቅ የቢዝነስና የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች ዳኝነት በሁለት ምዕራፍ ሲያወዳድርበት የቆየ ሲሆን ባንካችንም የሁለተኛው ዙር የፍፃሜ ውድድር የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ነበር። ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ስምምነቱ ሁለቱም ተቋማት አገር የመገንባት የጋራ አላማ ያላቸው እንደመሆናቸው በጋራ የሚሰሯቸውን ቀደም ብለው የተጀመሩ የሥራ ግንኙነቶች የሚያጠናክር እንደሚሆን ገልፀዋል። የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ለሀገር ችግር ፈቺ ሃሳቦች በሀገር ልጆች የሚቀርቡበት በመሆኑ ባንኩ ፕሮግራሙን ለማገዝ መወሰኑን ፕሬዚዳንት አቤ ተናግረዋል። ፕሮግራሙ በሚጠበቀው ልክ በፍትሃዊ ዳኝነት ትክክለኛ ችግር ፈቺ ሃሳቦች የሚያሸንፉበት እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው ነጋድራስ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆንና የቢዝነስ ሃሳቦቹ ወደተጨባጭ ዉጤቶች እንዲቀየሩ የባንኩ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ሦስተኛው ዙር 'ነጋድራስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነጋድራስ የስራ ፈጠራ ውድድር' በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከእሁድ ሕዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚተላለፍ ይሆናል።