ከተቀናጀ የስራ ላይ ሥልጠና ፕሮግራም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በዕውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እየሩሳሌም አመሃ በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የተካሄደውን የዕውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር በንግግር በከፈቱበት ወቅት እደተናገሩት፣ የተቀናጀ የሥራ ላይ ስልጠና ፕሮግራም የባንኩን የስልጠና አካሄድ በመለወጥ አይነተኛ ሚና አለው፡፡ ወ/ሮ እየሩሳሌም በቦሌና ቂርቆስ ዲስትሪክቶች በተመረጡ ቅርንጫፎች በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የተጀመረው ሥልጠና በሌሎች ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች እንዲሁም የስራ ሂደቶች ጭምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የአሰልጣኞች ሥልጠና ወስደው በተቀናጀ የስራ ላይ ሥልጠና ፕሮግራም የተሳተፉ ባለሞያዎች የባንኩን የሰው ኃይል ልማት መርኃ ግብር በመተግበር ትልቅ አቅም መፍጠራቸውንም ነው ወ/ሮ እየሩሳሌም የተናገሩት፡፡ በዕውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ በበኩላቸው የተቀናጀ የሥራ ላይ ሥልጠና የባንክ ሥራ የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተቀናጀ የሥራ ላይ ሥልጠና ትክክለኛ የክህሎት ማስጨበጫ አማራጭ እንደሆነ በጥናት ጭምር መረጋገጡን የገለፁት ዶ/ር ገመቹ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንኑ ተሞክሮ በአግባቡ እየተገበረ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊ ሠራተኞች በበኩላቸው የተቀናጀ የሥራ ላይ ሥልጠና ከተደራሽነቱ፣ ከወጥነቱና ከወጪ ቆጣቢነቱ እንዲሁም በሥራ ቦታ ተግባር ተኮር ክህሎትና ዕውቀት ከማስተላለፍ አንፃር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዕውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ በተቀናጀ የሥራ ላይ ሥልጠና በአሰልጣኝነት ለተሳተፉ ባለሞያዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን፣ ሥልጣናው ያስገኛቸው ውጤቶችና በቀጣይ በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸው ተግባራትን የሚያመላከት የዳሰሳ ጥናትም ቀርቧል፡፡