ሰሞኑን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የተፈረመው ይህ ስምምነት 26 የሚሆኑ የፌዴራል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እና በስራቸው የሚገኙ 360 ተቋማት ለተገልገዮች የሚሰጧቸው አገለግሎቶችን ክፍያ በዲጂታል አማራጭ የሚቀበሉበትን መንገድ ያመቻቸ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የባንኩ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገ/ማሪያም የተፈረመው ስምምነት ተቋማቱ ክፍያቸውን በሲቢኢ ብር አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፣ ይህ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ ለአጠቃቀም ምቹ እና ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ በመሆኑ ህብረተሰቡ በስፋት እንዲጠቀምበት ጠይቀዋል፡፡ አቶ ወጋየሁ ባንኩ ቀደም ሲልም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ተመሳሳይ የሥራ አጋርነት ከሌሎች የመንግስትና መንግስታዊ የልሆኑ ተቋማት ጋር መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ ዶ/ር ይሽሩን አለማየሁ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ የመንግስትን አሠራር ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነውን የመንግስት የክፍያ ስረዓት ዲጂታላይዝ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ይሽሩን፣ ይህም ግልፀኝነትን፣ ፍትሀዊነትን እና ቀልጣፋ አሠራርን በማስፈን ለመልካም አስተዳደር መጎልበት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል ፡፡ ከፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ዕለት ጀምሮ ሁሉም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እና በስራቸው የሚገኙ ኤጀንሲዎች ሲቢኢ ብርን በመጠቀም ክፍያቸውን መሰብሰብ እንደሚችሉ ታውቋል ፡፡