የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በደንበኞች አገልግሎት ወር መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ለደንበኞች ያስተላለፉት መልዕክት፡፡

"በመላው ሀገራችን የሚገኙ ደንበኞቻችን ለባንካችን እድገት እና ዘላቂነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ታላቅ አክብሮት አለን፡፡ ከባንካችን ጋር ሰለሚሠሩም እናመሰግናለን፡፡ ባንካችን የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የደንበኞቻችን ደስተኛነት የእድገት ጉዟችን መሰረት በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በመስጠት የላቀ እርካታ እንድታገኙ ዘወትር እንተጋለን፡፡ የባንካችን ደንበኞች ብቻ ሳትሆኑ ቤተሰብም በመሆናችሁ ስለአገልግሎት አሰጣጣችን የምትሰጡንን ሀሳብ እና አስተያየት አክብረን እንቀበላልን፡፡ ለተግባራዊነቱም አበክረን እንሠራለን፡፡ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ከናንተ ከደንበኞቻችን ጋር በመሆን ወደምቹ አጋጣሚ እየቀየርን እድገታችንን እናስቀጥላለን፡፡ በላቀ የደንበኞች አገልግሎት የባንካችንን ስምና ዝና በመጠበቅ ዘወትር የሚተማመኑበት ባንክ ሆኖ እንዲቀጥል ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ቀዳሚ ሆኖ በማገዝ ዘመናዊ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለደንበኞች ምቹ የሆኑ አገልግሎቶችን በማቅረብ በባንክ ኢንዱስትሪው የሚገጥመንን ብርቱ ውድድር በመሪነት ለመወጣት እንተጋለን፡፡ ክቡራት እና ክቡራን ባንካችን እናንተን ደንበኞቻችንን ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃችኋል፡፡ ስለምናገለግላችሁ ደስተኛ ነን፡፡ ዛሬም ቢሆን ደንበኝነታችሁን አጠንክራችሁ ከባንካችን ጋር እንድትሠሩ አጥብቀን እንሻለን፡፡ እኛም ፍላጎታችሁን ለማሟላት እና ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ በመጨረሻም ውድ ደንበኞቻችን ባንካችን ዛሬ ለደረሰበት ስኬት ስላበቃችሁን እያመሰገንኩኝ በመጭው ጊዜም አብራችሁን በደንበኝነት እንድትዘልቁ አደራ እላለሁ፡፡ በድጋሜ መልካም የደንበኞች አገልግሎት ወር እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!"