በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዋናው መስሪያ ቤት በተዘጋጀው የደንበኞች አገልግሎት ወር ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካስተመር ኤክስፔሪያንስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ እንደተናገሩት የደንበኞች እርካታ የስኬት ሁሉ መሠረት እንደሆነ ባንኩ እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡ ደንበኞቻችን የስኬታችን መሠረት መሆናቸውን አጉልቶ ለማሳየት እና ምስጋና ለማቅረብ፣ እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ በመላበስ የአገልግሎት አሰጣጥ ባህላችንን በማጎልበት ቀልጣፋ እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ቃል ለመግባት የደንበኞች አገልግሎት ወር እንደሚከበር አቶ ኃይለየሱስ ገልፀዋል፡፡ አቶ ኃይለየሱስ በቀጣይ የደንበኞች አገልግሎት ወር ከአለም አቀፍ የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት ጋር በማስተሳሰር በየዓመቱ በጥቅምት ወር በተጠናከረ ሁኔታ በባንኩ እንደሚከበር ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ጌታቸው በመርሀ ግብሩ ላይ በመገኘት የባንኩን ሠራተኞች በመወከል የእንኳን አደርሳችሁ መልእክት አስተላፈው፣ ለባንኩ ደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ደንበኞችን በትጋት፣ በታማኝነት እና በቅንነት በማገልገል የባንኩን ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ የገለፁት አቶ ጌታቸው ፣ የአገልጋይነት መንፈስ የባንኩ መለያ እንዲሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::