ለ አንድ ወር ከሚቆየው የደንበኞች አገልግሎት ወር ጋር ተያይዞ በወጭ ንግድ ከተሰማሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ በርካታ ደንበኞች የተገኙ ሲሆን፣ ባንኩ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ እና መሻሻል ማምጣቱን ገልፀው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ባንኩ በቀጣይ ሊያሻሽላቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን፣ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፍቅረስላሴ ዘውዱ፣ የዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ማክዳ ኡመር እና የሆል ሴል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቦኩ ቤኛ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የብድር ማስያዣ ንብረት ግምት፣ የብድር አሰጣጥ ሂደት፣ ለወጭ ንግድ የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ሌሎችም በውይይቱ ትልቅ ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ውይይቱ ባንኩ በቀጣይ ሊያሻሽላቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ግብአት ያገኘበት እና ደንበኞችም በባንኩ አሠራር እና መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ ያገኙበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ከደንበኞች ጋር የሚደረገው ውይይት በሌሎች ዘርፎች ከተሠማሩ የባንካችን ደንበኞች ጋርም ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል፡፡