ዛሬ ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም በመቐለ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የደንበኞች ወር የውይይት መርሐ ግብር መክፈቻ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጦርነት ምክንያት የተዳከመውን የትግራይ ክልል ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የጀመራቸው ስራዎች አበራታች ነው። በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ቀደመው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነቱ ለመመለስ የጀመራቸውን ጥሩ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ባንኩ በክልሉ ልማት እንቅስቃሴዎች በመደገፍ ማህበራዊ ሐላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ያሉት አቶ ጌታቸው የትግራይ ኢንቨስትመንት በማጠናከር የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ስራ ለማስገባት በክልሉ የንግድ ማህበረሰብ የሚነሳው የብድር አቅርቦት ጥያቄዎችን አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጥ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ጥያቄዎች ለመመለስና ለመወያየት እንዲህ አይነት መድረክ ማዘጋጀቱ የሚመሰገን መሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደርም ባንኩ ስራዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ልሳነወርቅ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹ ፍላጎት ለማርካት ዘላቂነት እና ተከታታይነት ያለው የማሻሻያ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታማኝነት አብረውት የዘለቁ ደንበኞችን ሁሉ በታላቅ አክብሮት ያመሰግናል ያሉት አቶ ኤልያስ ወደፊትም አብረውት እንዲዘልቁ አደራ ብለዋል። ባንካችን ደንበኞችን ይበልጥ ለማርካት ተግቶ ይሠራልም ብለዋል አቶ ኤልያስ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ 10 ከተሞች ማለትም መቐለ ፣ ሽረ ፣ አዳማ ፣ ድሬዳዋ ፣ ሰመራ ፣ ጂማ ፣ ሀዋሳ ፣ ሻሸመኔ ፣ ጅግጂጋ እና ወላይታ ሰዶ "የላቀ አገልግሎት ፣ ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ቃል የጀመረው የደንበኞች ወርን ምክንያት በማድረግ ከደንበኞች ጋር እየተወያየ ይገኛል።