በሀዋሳ ከተማ ከደንበኞች ጋር በተካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃብት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ የሀዋሳ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ወየሣ ጥላሁንና የዲስትሪክቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም የባንኩ የትኩረት አቅጣጫ የደንበኞችን አገልግሎት ማሻሻል መሆኑን ገልፀው፣ ባንኩ ደንበኛን ያማከለ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከደንበኞች ጋር ተቀራርቦ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ አፍሬም፣ በባንኩ እየተከበረ የሚገኘው የደንበኞች አገልግሎት ወር እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከደንበኞች ጋር በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ የሚገኘው የውይይት መድረክ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም የውይይት መድረኮቹ የባንኩን አሠራሮች እና አገልግሎቶች ለደንበኞች በግልፅ ለማስረዳት እንዲሁም ለቀጣይ መሻሻል ከደንበኞች ግብአት መውሰድን አላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የሀዋሳ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ወየሣ ጥላሁን በበኩላቸው የደንበኞች አገልግሎት ወር እየተከበረ የሚገኘው ደንበኞቻችን የስኬታችን መሰረት መሆናቸውን በማመን መሆኑን ገልፀው፣ ደንበኞቻችንን በከፍተኛ የአገልግሎት ስሜት ለማስደሰት ቃላችንን የምናድስበት ጭምር ነው ብለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት ደንበኞች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን በቂ ማብራሪያ እና ምላሽ አግኝተዋል፡፡