በዲላ ዲስትሪክት አዘጋጅነት በተካሄደው የደንበኞች የውይይት መድረክ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቁጠባ ባህልን በማዳበር እና የብድር ስርዓትን በመዘርጋት የሀገሪቱ ሀብት እንዳይባክን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡ ዶክተር ዝናቡ ባንኩ በዞኑ በርካታ አከባቢዎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በቀጣይም ተደራሽነቱን እንዲይሰፋ ጠይቀዋል፡፡ በብድር አሰጣጥ በኩል ባንኩ በያዝነው ዓመት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ዶ/ር ዝናቡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ባንኩ እየሰጠ ላለው አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ አለሙ ከባንኩ ጋር በታማኝነት የሚሠሩ ደንበኞችን አመስግነዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ ባንኩ ዘመናዊ እና የላቀ የባንክ አገልግሎቱን በማስፋት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እየሠራ መሆኑን ገልፀው፣ ከደንበኞች የሚሰጡ አስተያየቶች እና ጥቆማዎች ለቀጣይ መሻሻል እንደግብአት እንደሚጠቅሙ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲላ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ከበደ በበኩላቸው ባንኩ በባለፉት ሶስት አመታት ደንበኛ ተኮር የሪፎርም ስራዎችን ሲያከነውን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ደንበኞች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ አቶ ሙሴ የዲስትሪክቱ ተቀማጭ ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልፀው፣ ባለፉት ስድስት ወራትም ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ ደንበኞች በብድር አሰጣጥና አመላለስ፣ ባንኩ በሚያወጣቸው አዳዲስ አሠራሮች እና መመሪያዎች፣ በባንኩ በመካሄድ ላይ ባለው ሪፎርም እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ላነሱት ሃሳብ እና አስተያየቶች የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።