የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዋናው መስሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሀ ግብር የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለበይክ ሙዳራባህ የተሰኘ አዲስ የሲቢኢ ኑር የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት ያስተዋወቀ ሲሆን፣ 3ኛውን ዙር "ሐጅ ለሁሉም" የንቅናቄ መርሃ ግብርም በይፋ አስጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን በመርሀ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ባንኩ ባለፉት 10 ዓመታት የሙስሊሙን ማሕበረሰብ ፍላጎት ያማከሉና የሸሪዓ መርሆዎችን የተከተሉ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ጊዜ ከ1915 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎቹ በተለየ መስኮት እንዲሁም በ147 የሲቢኢ ኑር ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ከባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ ኑሪ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኑሪ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የጀመረበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፉት ሁለት ወራት የሙዳራባህ የኢንቨስትመንት ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ንቅናቄ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ከ3.5 ቢልዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብና ከ80 ሺ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራች ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት በማድረግ እየሰጣቸው ከሚገኙት አገልግሎቶች መካከል አንዱ ‘ለበይክ’ የተሰኘ የሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች ወጪያቸውን ለመሸፈን ቁጠባ የሚያደርጉበት የተቀማጭ ሂሳብ መሆኑን የገለፁት አቶ ኑሪ፣ ባንኩ በአሁኑ ጊዜም ለበይክ ሙዳራባህ የተሰኘ አዲስ የሲቢኢ ኑር የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አብስረዋል፡፡ አቶ ኑሪ ጨምረው እንደገለፁት በሚቀጥሉት 30 ቀናት በሚካሄደው ‘’ሐጀ ለሁሉም’’ ንቅናቄ አገልግሎቱን በማስተዋወቅ እና ሌሎች መርሀ ግብሮችን በማካሄድ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሐጅ የማድረግ ንያቸውን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ ኮሚቴ አባል ዶክተር መሐመድ ዘይን በበኩላቸው ከዚህ ቀደም አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም የሐጅ ስነ-ስርዓትን ለመከወን ይቸገር እንደነበር በመግለፅ ባንኩ እነዚህን አገልግሎቶች ተግባራዊ ማድረጉ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ የፈጣሪውን ጥሪ ምላሽ እንዲሰጥ አስችሎታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሃገር ሃብትና መገለጫ ነው ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዝደንት ተወካይ ኡስታዝ አቡበከር፣ ሐጅ ከእስልምና ዕምነት መሰረቶች አንዱ ሲሆን የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ ለማሳካት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁሉም ባንኮች በመቅደም ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ በህዝበ ሙስሊሙ ስም ከልብ አመስግነዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ሃላፊዎች፤ የባንኩ የሸሪዓ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ ባንኩ ባዘጋጀው የሙዳራባህ የኢንቨስትመንት ተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰብ ንቅናቄ ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች የማበረታቻ እና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ6 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እና ከ90 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ አገልግሎቱ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡