የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 218.2 ቢሊዮን ብር ብድር አቅርቧል፡፡
ባንኩ 208.8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት አቅዶ 218.2 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት የዕቅዱን 104.5 ከመቶ መፈፀም ችሏል፡፡ የባንኩ የስትራቴጂና ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ነቃህይወት እንዳብራሩት ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 198.3 ቢሊዮን ብር ብድር ለግሉ ዘርፍ 20 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመንግስት የተለያዩ ዘርፎች አቅርቧል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጀት ዓመቱ ብቻ 120.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ በማሰባሰብ የባንኩን አጠቃላይ ተቀማጭ መጠን 1.2 ትሪሊዮን ብር ማድረሱን ዳይሬክተሩ አቶ ዘላለም በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡ እንደሪፖርቱ ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 85 ቢሊዮን ብር ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም 37.7 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከመንግስት ዘርፍ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሃብቱን 1.43 ትሪሊዮን ብር ማደረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጀመረው ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን በዋና ዋና የፋይናንስ ነክ እና ፋይናንስ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ይመክራል፡፡