የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ፖሊስን ጠቅሶ እንደዘገበው "ሎተሪ ደርሶዎታል" በማለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስም ስልክ በመደወል የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው፡፡ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች የግል ተበዳይ ለሆኑት ለአቶ ድሪባ ለገሰ ‘‘ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ነው የምንደውለው፣ እድለኛ ነዎት፣ እንኳን ደስ አለዎት፣ ሎተሪ ደርሰዎታል'' በማለት እንደደወሉላቸው ዘገባው ያስረዳል፡፡ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት‘‘የምንነግርዎትን ቁጥሮች ይንኩ'' የተባሉት የግል ተበዳይ በስልክ የተገለፀላቸውን ትእዛዝ ከፈፀሙ ከደቂቃዎች በኋላ ከባንክ አካውንታቸው ላይ 99 ሺህ ብር መቀነሱን የሚገልጽ መልዕክት በስልካቸው ዘገባው ያስረዳል፡፡ የግል ተበዳይ እንደተታለሉ ሲገነዘቡ በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለጎማ ቁጠባ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ፖሊስ ምርመራውን ጀምሯል፡፡ ፖሊስ ለግል ተበዳይ የተደወለበትን ስልክ መነሻ በማድረግ ማስረጃ በማሰባሰብ ባደረገው ክትትል ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 አካባቢ የመጀመሪያውን ወይም ለግል ተበዳይ የደወለውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጎማ ቁጠባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል። እንደዘገባው ተጨማሪ ምርመራ በማስፋት ለወንጀሉ ተባባሪ የሆነ አንድ ተጨማሪ ግለሰብ ተይዟል። ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት በተደረገ ብርበራም ከዚሁ ግለሰብ መኖሪያ ቤት 89 የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ማህተሞች ያሉባቸው ልዩ ልዩ ሀሰተኛ ሰነዶች፣ 19 የተለያዩ የባንክ ደብተሮች፣ 7 ኤቲኤም ካርዶች፣ 5 የተለያዩ ግለሰቦች መታወቂያዎች፣ 6 ፖስፖርቶች እና 13 የሲም ካርድ ማቀፊያዎች መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።