![](/cbeapi/uploads/2_5d760d41bd.jpg)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ሰብስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ጉባኤ ላይ የባንኩ የስትራቴጂና ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ነቃህይወት ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ2023/24 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 878.5 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ሃዋላ ደግሞ 2.07 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በግዢ 286.1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ግኝት በባንኩ ተሰብስቧል፡፡ ከተሰበሰበው 3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ውስጥ 89.9 ሚሊዮን ዶላሩ በሲቢኢኑር አገልግሎት አማካኝነት የተሰበሰበ መሆኑንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ከውጭ ሃዋላ 2.18 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ የተሰበሰበው 2.07 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት 1.97 ቢሊዮን ዶላር ተሰብስቦ ነበር፡፡ ባለፈው አመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሰብስቦ እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መ/ቤት የመሰብሰቢያ ማዕከል ትላንት ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጀመረው አመታዊ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬም በቡድንና የጋራ ውይይት ቀጥሏል፡፡ ጉባኤው ካለፈው በጀት አመት አፈፃፀም በተጨማሪ በተያዘው በጀት አመት እቅድ ላይ እየመከረ ይገኛል፡፡