ከሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 (2023/24) በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 (2024/25) በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ ዓመታዊ ጉባኤ የቀጣይ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡ የባንካችን ፕሪዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በጉባኤው ማጠቃለያ መልእክታቸው የባንኩን የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች አመልክተዋል፡፡ የባንኩን ትርፋማነት ማረጋገጥ እና በዚህ ረገድ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ዋነኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አቶ አቤ ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ነው አቶ አቤ የተናገሩት፡፡ ደንበኛን ማእከል ባደረገ አሠራር የደንበኛ ግንኙነት እና አያያዝ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አቶ አቤ ያነሱት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ዲጂታል አገልግሎቶችን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ ከቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ሆኖ በአቶ አቤ ተነስቷል፡፡ የስጋት ምንጮችን በመለየት እና ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት የባንኩን፣ የደንበኞችን እና የሠራተኛውን ደህንነት መጠበቅ እንዲሁ አቶ አቤ በዋና የትኩረት አቅጣጫነት ያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ሁሉም የባንኩ ሠራተኛ አሁን በባንኪንግ አንዱስትሪው የሚታየውንም ሆነ በቀጣይ ከውጭ ሀገር ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ፉክክር በሚገባ በመዘጋጀት እና ምላሽ በመስጠት የባንካችንን የገበያ ድርሻ ማስቀጠል እና ማሳደግ እንደሚገባ አቶ አቤ አደራ በማለት ስብሰባውን ዘግተዋል፡፡