የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት ተሸላሚ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ/ም በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት የአቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት የዳይመንድ ደረጃ ልዩ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ ስኬታማ ተሳትፎ ላደረጉ ተቋማት እና አመራሮች ሽልማት የሚያበረክተው አቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት ድርጅት ከ75 ዓመታት በላይ የአገልግሎት ቆይታ ላላቸው እና በቆይታቸው ለተከታታይ ጊዜ ትርፋማ እና ስኬታማነትን ላስመዘገቡ ተቋማት እና ተቋማቱን በብቃት ለመሩ አመራሮች የሚሰጠውን ሽልማት ነው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ለባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የሰጠው፡፡ አቶ አቤን በመወከል በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ከአቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት የበላይ ጠባቂ ከሆኑት የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት ዶ|ር ሙላቱ ተሾመ እጅ ሽልማቱን ተረክበዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም እንዳሉት ሽልማቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሀገራችን የምጣኔ ሀብት ጉዞ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚገልፅ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሀገራዊ ሽልማት ባንኩ በቀጣይ ለሚኖረው ሥራ ጥንካሬ ይሰጠዋል ያሉት አቶ ኤፍሬም ባንኩ ያለው ጠንካራ የሰው ኃይል ለባንኩ ስኬት መሰረት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም ለሁሉም የባንኩ የሥራ አመራሮች እና ሠራተኞች የእንኳን ደስ አለን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡