የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን ሕንጻ በጋራ ባለቤትነት ለማልማት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተፈራረሙ፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ዋና መ/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የማህበሩ ቦታ ላይ የሚለማው ይኸው ሕንጻ ከ15.5 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚፈጅ ተገምቷል፡፡ ስምምነቱን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚደንቱ አቶ አቤ ሳኖ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ደግሞ ፕሬዚደንቱ አቶ አበራ ቶላ ፈርመዋል። በፊርማ ሥነ - ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚደንት አቶ አቤ ሳኖ እንደተናገሩት ከ14.4 ቢሊየን ብር በላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የሚሸፈን ሲሆን፤ ቀሪው 1.1 ቢሊየን ብር በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ይሸፈናል፡፡ ሕንጻውን ከ4 እስከ 5 ዓመታት ሠርቶ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡ የሚለማውን ሕንጻ ከአካባቢው መስህብነት እና ውበት ጋር ለማጣጣም የዲዛይን ክለሳ ሥራዎች እንደሚሰሩም አቶ አቤ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ እንደገለጹት ስምምነቱ ሁለቱንም ወገኖች የሚጠቅም ነው፡፡ ‹‹ሁለቱም ተቋማት የህዝብ ናቸው፡፡ የሚሰሩትም ለአንድ ዓላማ ነው፡፡›› ያሉት አቶ አበራ ማህበሩ ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ቀውሶችን ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያ በመስጠቱ፤ ሕንጻውን ለማሰራት የአቅም ውስንነት አጋጥሞታል ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በዛሬው ዕለት የተደረገው ስምምነትም የማህበሩን ሕንጻ በጋራ ባለቤትነት በማልማት ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡