የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ11.7 ሚሊዮን በላይ ደረሰ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ብር ፕላስ (CBE Birr Plus) በሚል በአዲስ መልክ አሻሽሎ ያቀረበውን የሲቢኢ ብር አገልግሎት መተግበሪያ ዛሬ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የመሰብሰቢያ ማዕከል በይፋ ሥራ አስጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ የተሻሻለው መተግበሪያ ይፋ በተደረገበተ መርሀ ግብር ላይ እንደተናገሩት የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ11.7 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ አቶ ኤፍሬም ባንኩ በሰኔ 2009 ዓ.ም የሲቢኢ ብር አገልግሎትን እንደ አንድ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጭ እንደጀመረ ገልፀው፣ አገልግሎቱን በየጊዜው በማሻሻል የተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገራችን ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን በግምባር ቀደምትነት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ ባለፈው በጀት ዓመት በባንካችን በኩል ከተፈፀመ በቁጥር ከ1.56 ቢሊዮን የሚበልጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም በገንዘብ ከ 31.6 ትሪሊዮን ብር በላይ ውስጥ በባንኩ ዲጂታል አገልግሎት አማራጮች የተፈፀመው 72 ከመቶ ድርሻ መያዙን ገልፀዋል፡፡ ጥሬ ገንዘብ አልባ ግብይትን እውን ለማድረግ የሲቢኢ ብር አገልግሎት እጅግ ጉልህ ሚና እንዳለው አቶ ኤፍሬም ገልፀው፣ ይህን መነሻ በማድረግ ባንኩ የሲቢኢ ብር አገልግሎቱን በየጊዜው እያሻሻለ እንደመጣ አመልክተዋል፡፡ ባንኩ በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ያስጀመረው ‘የሲቢኢ ብር ፕላስ’ መተግበሪያ በርካታ አገልግሎቶችን በማካተት ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ ተደርጎ ተሻሽሎ የቀረበ መሆኑን የገለፁት አቶ ኤፍሬም፣ ሁሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታ ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገብረ ማሪያም በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ንግግራቸው ባንኩ በሁሉም መስኮች በግምባር ቀደምትነት እየመራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ከሚያደርገው ጥረት ጋር ተያይዞ በሞባይል መኒ አገልግሎት ያለውን የገበያ ድርሻ አጠናክሮ ለመቀጠል የሲቢኢ ብር መተግበሪያውን በአዲስ መልክ አሻሽሎ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወ/ሮ ትግስት ሀሚድ ባንኩ በዲጂታል አገልግሎት መሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ እንደ አንድ የፋይናስ ተቋም የዲጂታል አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ወ/ሮ ትግስት፣ ለዚህም ባንኩ የሚያቀርበውን ዲጂታል አገልግሎት በየጊዜው በማሻሻል ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ባንኩ አዲስ ያቀረበው የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያ በሚገባ በባለሙያ ተፈትሾ ደህንነቱና አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ወ/ሮ ትግስት ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ ትእግስት የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያ በውስጥ አቅም የተሠራ መሆኑን አድንቀው በሥራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና በማቅረብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያን በይፋ ሥራ ማስጀመሪያ መረሀ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንካችን የቦርድ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች፣ ደንበኞች፣ የሥራ አጋሮች፣ የባንኩ ሠራተኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡