![](/cbeapi/uploads/photo_2024_08_02_17_08_37_2_f8eec95710.jpg)
የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የፕሬዚዳንቱ ተወካይና የሰው ኃይል ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው፡፡ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ከስምምነቱ በኋላ እንደገለፁት ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በጥናት እና ምርምር መስክ፣ በሰው ኃይል ልማት፣በቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ዘርፍ እንዲሁም የባንክና ፋይናንስ ዘርፉን በሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት ያስችላቸዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትን የመስጠት ግቡን ለማሳካት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን በስምምነቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፋይናንሱ ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይልን በማፍራት እና በምርምር ሥራዎች አይነተኛ ሚና እየተወጣ ያለ ተቋም ነው ያሉት አቶ ኤፍሬም ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብሮ መሥራት ሀገራዊ ውጤቱን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ288ሺ በላይ ምሁራንን ያፈራ እና ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ትልቅ አሻራ ያስቀመጠ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጀ ተወዳዳሪ የሚያደርጓት ተቋማት ያላት ሀገር ስለመሆኗ ማሳያ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ነው ብለዋል፡፡ የሁለቱ አንጋፋ ተቋማት በጋራ መሥራት እንደሀገር አቅምን አቀናጅቶ የተሻለ ነገን ለመፍጠር በእጅጉ እንደሚረዳ ተገልጿል ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ!