የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዳማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

• ስምምነቱ የውሃ ፍጆታ ክፍያን በሲቢብር ለመክፈል የሚያስችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የተፈረመው ይህ ስምምነት በአዳማ ከተማ የሚገኙ ደንበኞች ወርሀዊ የውሀ ፍጆታ ክያቸውን በሲቢኢ ብር ለመፈፀም የሚያስችላቸው ሲሆን፣ ይህም በከተማው ዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን ለማስፋፋት የተያዘው ዕቅድ አካል መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የባንኩ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገ/ማሪያም ሲቢኢ ብር ለአጠቃቀም ምቹ እና ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ ዲጂታል የክፍያ አማራጭ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የባንኩ የቅርንጫፍ እና ሪቴል ባንኪንግ ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ ባንኩ ቀደም ሲልም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ተመሳሳይ የሥራ አጋርነት ከሌሎች የመንግስትና መንግስታዊ የልሆኑ ተቋማት ጋር መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡ በስምምነቱ ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ ወሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ አብዱልጀሊል በበኩላቸው ከተማዋ እየደገችና እየሰፋች እንደሆነ በአሁኑ ጊዜም የአዳማ ከተማ ወሃና ፍሳሽ አገልግሎት ከ92 ሺ በላይ ደንበኞች እንዳሉት ገልፀው፣ ዲጂታል የክፍያ አማራጩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እና ክፍያዎችን በወቅቱ ለመሰብስብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡