"የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ቃል ከታህሳስ 24 እስከ ጥር 25፣ 2017 ለአንድ ወር የሚከበረው የደንበኞች አገልግሎት ወር የመክፈቻ መርሀ ግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት እና በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡ በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው የመክፈቻ መርሀ ግብር የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ሌሎች የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች፣ የባንኩ ደንበኞች፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የባንኩ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የተከበሩ አቶ አህመድ ሽዴ ደንበኞች የባንኩ ስኬት መሠረቶች በመሆናቸው ምስጋና ማቅረብ የደንበኞች አገልግሎት ወር ዋና አላማ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አቶ አህመድ ባንኩ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት የደንበኞች አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፣ “እምነታችሁን ስለሰጣችሁን እና ከባንካችን ጋር ስለምትሠሩ እናመሰግናለን’’ በማለት ለባንኩ ደንበኞች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ለደንበኞች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተግባራዊነቱን እየተከታተለ እንደሚገኝ አቶ አህመድ ገልፀዋል፡፡ የባንኩ አገልግሎቶች የደንበኞችን ፍላጎት ማእከል እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑን የገለፁት አቶ አህመድ፣ የባንኩን አገልግሎት አሰጣጥም የላቀ ለማድረግ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በባንኩ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ተግባር ወደመሬት አውርዶ ይበልጥ ለማፋጠን እና የተሻለ ለማድረግ የደንበኞች አገልግሎት ወር እንደሚከበር ገልፀዋል፡፡ የዘንድሮው የደንበኞች የአገልግሎት ወር "የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ቃል በሁሉም ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች እንደሚከበር የገለፁት አቶ አቤ፣ ወሩ ለስኬታችን መሠረት የሆኑት ደንበኞች የሚመሰገኑበት እና ከደንበኞች ጋር ያለን ግንኙነት ይበልጥ የሚጠናከርበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ጥራት ማለት የደንበኞች እርካታ ማለት መሆኑን በመግለፅ መልእክታቸውን ማስተላለፍ የጀመሩት የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ መብራት፣ የባንኩን አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡