የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 25 እና 15 ዓመት ላገለገሉ ሠራተኞች ሽልማት እና ዕውቅና ሰጠ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በተከናወነ ሥነ ስርዓት ባንኩን ለ25 እና 15 ዓመት ላገለገሉ 392 የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የወርቅ የደረት ፒን ሽልማት እና የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቷል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የ15 ዓመት፣ እንዲሁም የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ የ25 ዓመት አገልግሎት ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለተሸላሚ ሠራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ እና ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ አቶ አቤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው ዓላማው ኢትዮጵያን ማገልገል መሆኑን ገልፀው፣ በርካታ ባንኩ ያሰለጠናቸው ሠራተኞች በተለያዩ ባንኮች በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ለ15 እና 25 ዓመት ባንኩን ማገልገል ትልቅ አርአያነት እንዳለው የገለፁት አቶ አቤ፣ አዲሱ ትውልድ ተቋም የመገንባት እና የመጠበቅ ክህሎት ረጅም ልምድ ካላቸው ሠራተኞች ሊወስድ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የባንኩ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው እንደተናገሩት በጥቂት ሠራተኞች ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትውልድ ቅብብል ስኬታማ ጉዞ አድርጎል። አቶ ኤፍሬም ባንኩ በአሁኑ ጊዜ ከ80 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን የያዘ አንጋፋ ተቋም ለመሆን መብቃቱን ገልፀዋል። የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ኃይል እና ጉልበት እንዲሆን እና የባንኩ ውጤታማነት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሠራተኞች ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ባንኩን 25 እና 15 ዓመት ላገለገሉ ሠራተኞች ዕውቅና እንደሚሰጥ አቶ ኤፍሬም ገልፀዋል፡፡