በባሌ ጎባ የተደረገው የደንበኞች የውይይት መድረክ
ባሌ ጎባ ከደንበኞች አገልግሎት ወር ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ጋር የውይይት መድረክ ከተካሄደባቸው ከተሞች አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሚደቅሳ ቶሎሳ፣ የባሌ ሮቤ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሙዲን ገመዳ እና ሌሎችም የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በዚህ የውይይት መድረክ በመገኘት ለደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን ደግሞ የውይይት መድረኩ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡ አቶ ዲኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ እና የሀገር ባለውለታ አንጋፋ ባንክ መሆኑን ገልፀው የደንበኞች የውይይት መድረኩን ማዘጋጀቱም የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ዲኖ ህብረተሰቡ ከባንኩ ጋር እንዲሠራ እና የቁጠባ ባህሉንም እንዲያዳብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ ደንበኞች ባንኩ አጠናክሮ ሊቀጥልባቸው የሚገቡ እንዲሁም ሊያሻሽላቸው እና በቀጣይ ሊሠራባቸው የሚገቡ ያሉዋቸውን ጉዳዮች አንስተው በባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡