የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ይበልጥ ተቀራርበው መሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።

"የላቀ አገልግሎት ፤ ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ቃል የደንበኞች አገልግሎት ወርን በተለያዩ ኹነቶች እያከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በወለይታ ሶዶ ከተማ ተገኝቶ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅርንጫፍ እና ሪቴይል የባንክ አገልግሎት ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ምእራብ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ እና የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የክልሉን የልማት ሥራዎችን ይበልጥ መደገፍ በሚችልባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ፤ በርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ምክክር አድርገዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ በቱሪዝም፣በግብርና፣በብድር አቅርቦት እንዲሁም በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጠውን የባንክ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅርንጫፍ እና ሪቴይል የባንክ አገልግሎት ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ በበኩላቸው በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመሥራት የቀረበው ፍላጎት ትክክል መሆኑንና በተለይም በተደራሽነት በኩል ባንኩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፤ የዲጅታል ባንክ አገልግሎት አማራጮችን በስፋት ለማቅረብ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የወላይታ ሶዳ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አላሎ በበኩላቸው ዲስተሪክቱ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጋር በቅርበት በመሥራት የተነሱትን ጉዳይች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁሉም ዲስትሪክት ድ/ቤቶችና በተለያዩ ከተሞች "የላቀ አገልግሎት ፣ ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ቃል የደንበኞች አገልግሎት ወርን እያከበረ ይገኛል፡፡