ሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024 በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የሪቴይል የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገብ በ ‘’Best Islamic Retail Banking Widow for Service Quality and Operations in Ethiopia 2024’’ ዘርፍ ካምብሪጅኢፋ /CAMBRIDGEIFA/ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ዱባይ ከተማ በተዘጋጀ መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡ አቶ አቤ ሳኖ በሥነ -ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በሽልማቱ ክብር እንደተሰማቸው ገልፀው፣ በቀጣይ በወለድ ነፃ አገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእምነት ምክንያት ከባንክ አገልግሎት ርቆ የነበረውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የሸሪአ መርህን መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10 ዓመታት በፊት መስጠት መጀመሩን አቶ አቤ አስረድተዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ባንካችን የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አቤ፣ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ዲጂታል አገልግሎቶችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ በማቅረብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ አቤ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ባንካችን በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ በተቀማጭ ገንዘብ 52 በመቶ፣ በፋይናንስ አቅርቦት 50 በመቶ እንዲሁም በደንበኛ ብዛት 32 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዋፅኦ በቁጥር ብቻ እንደማይገለፅ የተናገሩት አቶ አቤ፣ ወደፊትም በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነት ላይ ጠንክሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አግልግሎቱ እ.ኤ.አ በ2023 በሳውዲ አረቢያ ጂዳ በተካሄደው 9ኛው ዓለም አቀፍ ኢስላሚክ ሪቴል ባንኪንግ የሽልማት መርሀ ግብር በሪቴል ኢስላሚክ ባንኪንግ በኢትዮጵያ ተስፋ የተጣለበት ባንክ ተብሎ ሽልማት የተበረከተለት መሆኑ ይታወሳል፡፡