ባንካችን በስፓርቱ ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባደረገው ድጋፍ እና ታይትል ስፖንሰርነት በእንጦጦ ፓርክ የሚደረገው ወርሃዊ የሩጫ ውድድር ተተኪ ስፓርተኞችን እና ምርታማ ዜጋን ለማፍራት እንደሚያስችል ተገልጿል። ጉዳዩን በማስመልከት ዛሬ በባንካችን ዋና መስሪያ ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች አንዱ የስፖርቱን ዘርፍ መደገፍ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባንካችን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ታላቁን ሩጫ ስፖንሰር ማድረግ እንደጀመረ አቶ ደረጄ ገልፀው፣ የዚሁ የታላቁ ሩጫ አካል የሆነው “እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ” ስፖንሰር ሲያደርግ በደስታ መሆኑን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው የዚህ ዓይነት ስፖርታዊ ውድድር ለነዋሪው መገናኛ መድረክ ለመፍጠር እና ጤናን ለመጠበቅ እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡ ውድድሩ በወር አንድ ጊዜ ሳይሆን በየሳምንቱ ቢደረግ ውጤታማነቱ የጎላ እንደሚሆን የገለፁት ዶ/ር ሂሩት፣ የአካባቢውን ቅርስነት ለማቆየት፣ ለከተማው ውበት እና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት። ዶ/ር ሂሩት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ “ንቁ ፣ብቁ እና የይቻላል መንፈስን የያዘ ትውልድ” ለመፍጠር የያዘውን ርዕይ ለማሳካት እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች በጣም ጠቀሜታ እንዳላቸው አክለው ገልፀዋል። በእንጦጦ ፓርክ የሚካሄደው ይህ የሩጫ ውድድር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ወር በገባ የመጀመሪያው ቅዳሜ የሚደረግ የ5 ኪሜ ውድድር ሲሆን፣ በሚቀጥለው ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 የሚጀምር ሲሆን፣የመሳተፊያ ትኬት በሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያ ማግኘት እንደሚቻል ታውቋል።